የዳይሬክተሩ መልእክት የዳይሬክተሩ መልእክት

የተከበራችሁ ተገልጋዮቻችን በቅድሚያ እንኳን ወደ ባለስልጣኑ መ/ቤት አገልግሎት ለማግኘት በደህና መጣችሁ!

በትራንስፖርት ሚ/ር የትራንስፖርት ባለስልጣን የዜጎች ቻርተር ለተገልጋዮች የላቀ አገልግሎት ለመስጠትና በተቋማችን መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን ለማድረግ ቃል የምንገባበት ሰነድ ነው፡፡ የአገልግሎት ተጠቃሚዎቻችን ከባለስልጣኑ መ/ቤት ቀልጣፋና ውጤታማ አገልግሎት እንደሚጠብቁ በማመን ፍላጎታቸውን ለማሟላት አሰራራችንን ጥራቱን በጠበቀና ቀልጣፋ በሆነ መልኩ በማከናወን ህብረተሰቡን በከፍተኛ ደረጃ ለማገልገል ግብ አስቀምጠናል፡፡

ባለስልጣን መ/ቤቱ በአዋጅ የተቋቋመው በ1960 ዓ.ም የመንገድ ትራንስፖርት አስተዳደር በሚል ስያሜ ሲሆን፡ በተለይ ከ2005 ዓ.ም ወዲህ ተቋማዊ የሆነ መሰረታዊ የአሰራር ለውጥ እንዲመጣ ከመስራቱ በተጨማሪ በአገራችን የመንገድ ትራንስፖርት ዘርፍ እንዲስፋፋ፣ እንዲያድግና እንዲጠናከር ለማድረግ በርካታ ስራዎችን በመስራት መላው ህብረተሰቡን ተጠቃሚ እንዲሆን ተድርጓል፡፡ ከዚሁ በተጨማሪ በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ውስጥ የተቀመጡ የመንገድ ትራንስፖርት ዘርፍ ግቦች እንዲሳኩ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡

ባለስልጣን መ/ቤቱ ለተጠቃሚዎች የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት ለህብረተሰቡ በሚሰጣቸው አገልግሎቶች ላይ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት የህብረተሰቡን እርካታ ለማሳደግ ፅኑ አቋም አለው፡፡ በመሆኑም መ/ቤቱ በዜጎች ቻርተር ላይ ለተገልጋዮች የገባውን ግዴታ በተግባር ላይ ለማዋል ከህዝብና ከጭነት ትራንስፖርት፣ ከአሽከርካሪና ከተሸከርካሪ እንዲሁም ከሰሌዳ ጋር በተያያዘ የተቀመጡ አገልግሎቶችን በብቃት ለመወጣት ተገቢውን ጥረት ያደርጋል፡፡

ባለስልጣን መ/ቤቱ የሚሰጣቸው አገልግሎቶችና የአገልግሎት አሰጣጥ ደረጃ በዜጎች ቻርተር ውስጥ በግልጽ ተቀምጧል፡፡ በተቀመጠው የአገልግሎት አሰጣጥ ደረጃ መሰረት ተፈጻሚ መሆኑን ለማረጋገጥ እና የተቋማችንን የአገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል ለሚደረገው ጥረት የተገልጋዮቻችን አስተያየት እና ቀጥተኛ ተሳትፎ በእጅጉ ወሳኝ በመሆኑ ተገልጋዮቻችን የበኩላችሁን ድርሻ እንድትወጡ የአክብሮት ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡

የተገልጋዮቻችን እርካታ የስኬታችን መለኪያዎች ናቸው!!

 

አብዲሳ ያደታ

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር

 

ስለ ትራንስፖርት ባለስልጣን ስለ ትራንስፖርት ባለስልጣን