ዜና ዜና

የቃሊቲ አዉቶቡስ መነሀሪያን እና የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ማሰልጠኛ ማዕከልን ግንባታ ተጎበኘ

የቃሊቲ አዉቶቡስ መነሀሪያን እና የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ማሰልጠኛ ማዕከልን ግንባታ ተጎበኘ

የፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን አመራሮች በግንባታ ላይ ያሉትን የቃሊቲ አዉቶቡስ መነሀሪያን እና የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ማሰልጠኛ ማዕከልን ጎበኙ፡፡

ግንባታዎቹ የተጀመሩት ባለፈዉ አመት ሲሆን ተቋሙ እና የግንባታዉ አማካሪ ድርጅት የግንባታዎቹን ሂደት በተመለከተ በየጊዜዉ ሲገመግሙ ቆይተዋል፡፡

በወቅቱም የሁለቱም ፕሮጀክቶች ስራ ተቋራጮች ሪፖርት ያቀረቡ ሲሆን የቃሊቲ አዉቶቡስ መናሃሪያ ግንባታ 19.67% ላይ የደረሰ ሲሆን  የትራፊክ ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ማዕከል ግንባታ ደግሞ 17.57% መድረሱን አብራርተዋል፡፡

የተቋሙ አመራሮች የግንባታዉን ሂደት ከተመለከቱ በኋላ ከቃሊቲ አዉቶቡስ መናሃሪያ  እና የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ማሰልጠኛ ማዕከል ግንባታ ስራ ተቋራጮች ፣  አማካሪ ድርጅት ተወካዮች እንዲሁም  ከምህንድስና ባለሙያዎች ጋር   በግንባታዉ  ሪፖርት ዙሪያ ግምገማ አድርገዋል፡፡

የባለስልጣን  መ/ቤቱ አመራሮችም  ከቀረበዉ ሪፖርት መነሻ በማድረግ የመናሃሪያዉ ግንባታ ሂደት የተሻለ አፈፃፀም ላይ እንደሚገኝ አንስተው የማሰልጠኛ ማዕከሉ ግንባታ ግን መጓተት እንደሚታይበት ተናግረዋል፡፡

በጉዳዩ ዙሪያ የሁለቱም ግንባታ አማካሪ ድርጅት ተወካዮች አስተያየት የሰጡ ሲሆን በስራ ተቋራጮች በኩል በቂ የሰዉ ሃይል እና  ማሽነሪዎችን ከማቅረብ አንፃር ጉድለት እንዳለባቸዉ ጠቁመዋል፡፡

የስራ ተቋራጮችም ከአመካሪ ድርጅት ባለሙያዎች እና ከአሰሪ ተቋም አመራሮች ለተነሱት አስተያየቶች ምላሽና ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን የተጠቀሱት ችግሮች ስለመኖራቸዉ ተናግረው የሰው ሀይልን  በተመለከተ በኮቪድ-19 ምክንያት በበቂ ደረጃ ማግኘት እንዳልቻሉ የገለፁ ሲሆን ማሽነሪዎችን ከማሟላት አንፃር ጥረት እያደረጉ መሆናቸዉን ተንግረዋል፡፡ አክለዉም ተቋሙ  የሚጠየቀውን  ገንዘብ በሰዓቱ ቢለቅልን  በማለት  አስተያየታቸውን  ሰጥተዋል፡፡

የግንባታዎቹን አፈፃፀም ሪፖርት ግምገማ መድረክ ያጠቃለሉት የፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን የኮርፖሬት ዘርፍ ም/ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ አልማዝ በየሮ  የስራ ተቋራጮች የሰጡትን አስተያየቶች መሰረት በማድረግ  በቀጣይ ተግባራት  ዙሪያ አቅጣጫ አስቀምጠዋል፡፡

በዚሁ መሰረት የስራ ተቋራጮቹ ማንኛዉንም አማራጭ በመጠቀም ለግንባታዉ ሙሉ ትኩረት በመስጠት ግንባታዉን ማፋጠን እንዳለባቸዉ ተናግረዋል፡፡  ም/ዋና  ዳይሬክተሯ አክለዉም ግንባታዎቹ ለህብረተሰባችን በጣም ጠቃሚና ብዙ ችግሮችን የሚፈታ በመሆኑ ተቋማችን አስፈላጊዉን ዕገዛ  የማድረግ ስራ ይሰራል ብለዋል፡፡

 


የዜና ክምችት የዜና ክምችት