ዜና ዜና

የኤሌክትሮኒክስ ክፍያ አገልግሎት ሊጀመር ነዉ

የኤሌክትሮኒክስ ክፍያ አገልግሎት ሊጀመር ነዉ

 

የፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን በአሁኑ ወቅት በሀገራችን የተከሰተዉን የኮረና ቫይረስ ስርጭትን ለመቀነስና ንክኪን ለማስቀረት በመነሀርያዎች የሚሰራዉን የክፍያ ስርዓት ለማዘመን ከክፍያ ፋይናንሽያል ቴክኖሎጂ ሀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር እና ከህዝብ ትራንስፖርት ማህበራት ጋር በመተባበር የኤሌክትሮኒክስ ክፍያ አገልግሎትን በይፋ አሰጀመረ ፡፡

በወቅቱም የትራንስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ በመገኘት ንግግር ያደረጉ ሲሆን የህዝብ ትራንስፖርት ለሚደረጉ ጉዞዎች የኤሌክትሮኒክስ ክፍያ አገልግሎት ለማስጀመር መብቃቱ ትልቅ እምርታ እንደሆነ በመግለጽ ዘርፍን በቴክኖሎጂ ማዘመንና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት ዉዴታ ሳይሆን ግዴታ እንደሆነም አሳስበዋል ፡፡

የፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዲሳ ያደታ በበኩላቸዉ በህዝብ ትራንስፖርት የኤሌክትሮኒክስ ክፍያ አገልግሎት መጀመሩ ዘርፉ ወደ ቴክኖሎጂ የሚሸጋገርበት በመሆኑ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸዉ በመግለጽ የመንገድ ትራንስፖርት ዘርፉን ለማሻሻል ሁሉም ባለድርሻ አካል እጅ ለእጅ ተያይዞ በመስራት ለዉጥ ማምጣት እንደሚገባ ተናግረዋል ፡፡

በወቅቱ በቀረበዉ ሰነድ ላይ እንደ ተገለጸዉ በህዝብ ትራንስፖርት የኤሌክትሮኒክስ ክፍያ አገልግሎቱ መጀመር በዘርፉ ያሉ ህገወጥ ደላሎችን በማስቀረት በዘርፉ የተሰማሩ ማህበራትን የሚጠቅም ይሆናል፡፡ አገልግሎቱን ለማስጀመርም ከአስራስድስት/16/ ባንኮች ጋር በጋራ ለመስራት ከስምምነት ቢደረስም እስካሁን ባለዉ ከኢትዮጽያ ንግድ ባንክ ጋር መስራት እንደተጀመረ እና አንድመቶ /100/ኤጀንቶች ተከፍተዉ ለአገልግሎት እንደዋሉ ተገልጿል፡፡

ሲስተሙ የጉዞ መረጃዎችን ያካተተ በመሆኑ ማንኛዉም ተጓዥ ወደ መነሀርያ መሄድ ሳይኖርበት በግል ተንቀሳቃሽ ስልኩ የሚፈልገዉን አዉቶብስ ለመምረጥ ፣ ቀሪ ወንበሮችን ለማወቅ ፣ ጉዞ ሲሰረዝ ለማወቅ እና ሎሎችንም መረጃዎች ለማየት እንደሚረዳ ተገልጿል፡፡

 


የዜና ክምችት የዜና ክምችት